10/05/2024
Art is the source of all civilization!
ከጥንት እንጀምር። ግሪክ ነን። የማወራችሁ የኢኮኖሚ ቀውስ ክፉኛ ስለደቆሳቸው የሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ግሪካውያን አይደለም። የአለም ባንክ ወይም የአውሮፓ ህብረት ያበደራቸውን በመቶ ቢሊየን የሚቆጠር ዶላር መመለስ ስላቃታቸው ዘመነኞቹ አቴናውያን አይደለም። የለት ጉርሳቻውን መሸፈን አቅቷቸው ለት ተለት ለፉድ ስታምፕ ስለሚሰለፉት ግራ የተጋቡ ደቡብ አውሮፓውያን አይደለም።
የማወራው ከክርስቶስ ልደት በፊት ስለነበሩት የስልጣኔ አውራዎች ጥንታዊ ስፓርታውያን አቴናውያን ግሪካውያን ነው። መፅሀፉ "ፊተኞች ኋለኞች ፣ ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ" ያለው ተፈፀመ። እነዛ የፍልስፍና ጀማሪዎች እነዛ የኤፒክ ስነግጥም ጠበብቶች እነዛ የቲያትር ቀንዲሎች የሚቀጥለው ምግባቸው ከየት ዱብ እንደሚል የማያውቁ ምስኪኖች ሆኑ።
የዘመናችንን ግሪካውያን ዳግም እንርሳቸው፣ የጥንቱ ዜዉስ ይድረስላቸው። እኛ ከሄሮዱቱስ ፣ ሶቅራጥስ ፣ ሶፎክለስ ፣ ሆሜር ፣ አሪስጣጣሊስ፣ ሂፖክራተስ፣ ፓይታጎረስ፣ አርኪሜድስ ጋር ነን። በታሪክ ውስጥ የስነጽሑፍ ፍልስፍና ቲያትር የመጨረሻ ከፍታ ይኼው ዘመን ነበር። ስልጣኔውን አምጦ የወለደው ጥበቡ ነው። ፈላስፋዎች በአደባባይ ተገኝተው ይከራከራሉ። ታዳሚያን በትያትር አዳራሽ ታላላቅ ተውኔቶችን ይኮመኩማሉ። ተማሪዎች የሆሜርን ባለ 28,000 መስመር ግጥም ኢሊያድ እና ኦዲሴይን በቃላቸው ይወጣሉ። ዜጎች በየእለቱ በአደባባይ እየተገኙ በዲሞክራሲያዊ መብታቸው ዲሞክራሲያዊ ህይወት ይመራሉ። በየአራት አመቱ ደግሞ የኦሎምፒክ ስፖርትን እያዘጋጁ ይታደማሉ። ግሪካውያን ብዙ ሰጥተውናል―ዲሞክራሲን፣ የኦሎምፒክ ስፖርትን፣ ፍልስፍናን፣ ዘመናዊ ህክምናን፣ አልኬሚን(ለዘመናዊ ኬሚስትሪ መሰረት ነው)፣ ፊዚክስን(በተለይ አሪስጣጣሊስ) ፣ ሎጂክን(ሳይንሳዊ አመክንዮን) እስከዛሬ ድረስ የሚሰራ የነጠረ ከዘመን ዘመን የሚዘረዘር ጥበብን ሁሉ ቸረውናል። ነገር ግን ሁሉም ጥሩ ነገሮች ሁሉ መጨረሻ አላቸው። በትሮይ ጦርነት ትሮይ ተደመሰሰች። የግሪካውያን ስልጣኔ መጨረሻ ሆነ። ወደ ሮማውያን እንሻገር።
ሮማውያን ጦረኞች ናቸው። ከግሪካውያን የወረሱት እልፍ ነው። ሆሜር የግሪክ ትልቁ ገጣሚ ሲሆን ሮማዊው ቨርጂል ይህንኑ ኤፒክ ስነግጥም ዘዬ ተከትሎ "ኢሊያድ"ን የሚገዳደር ውብ ስንኝ "ኤኒድ"ን ፃፈ። ሌሎች ገጣሚዎችም አሉ እነ ኦቪድ። ነገር ግን ሮማውያን ሮማውያን እንጂ ሙሉ ለሙሉ የግሪካውያን ቅጂዎች አይደሉም። ሮማውያን የራሳቸውን አዲስ ዘዬ ፈጠሩ። ሮማውያን ተዋጊዎች ናቸው፤ የጦር ስልት አዋቂዎች ናቸው፤ ተስፋፊዎች ናቸው። አለም ታላቁን የእንግሊዝ ኢምፓየር አይቷል፤ ቤዛንታይንን አይቷል፣ መቄዶንያዊውን ትልቁ እስክንድርን አይቷል፣ ካርቴጂያዊው ሃኒባልን አይቷል፣ ፈረንሳዊውን ናፖሊዎን ቦናፓርትን አይቷል። እንደ ሮማውያን የተዋጣለት ጦረኛ ግን አላየም። አንድ አባባል "በእንግሊዝ ምድር ፀሐይ አይጠልቅም" ይላል። "በሮማውያን ምድር ግን ጦር አይጠልቅም" ሮማውያን ሁሌ እንደተዋጉ ነው፤ ደም እንዳፈሰሱ ነው፤ ግዛት እንዳስፋፉ ነው፤ ባሪያ እንደማረኩ ነው። ጦረኝነት ደማቸው ውስጥ ያለ ተፈጥሯቸው ነው። ይህ ታዲያ ከመሬት አልበቀለም፤ ዝም ብሎ አልመጣም። ጦረኝነት ዲሲፕሊን ይፈልጋል። እንከተለው። ሮማውያን ስልጡን ፖለቲከኞች ናቸው። ታላላቅ ኦራተሮች አሏቸው። ሮም ሪፐብሊክ ናት። ሪፐብሊኩን የሚመሩ ብዙ ሴናተሮች አሉ። ጁሊየስ ቄሳር መጥቶ ሪፐብሊኩን ወደ ኢምፓየር ቀየረው። ኤምፔሬሮቹ በዚህ በኩል ሃገር ይመራሉ፤ እልፍ ብለው ግዛት ያስፋፋሉ፤ ደሞ ወደ እልፍኛቸው ተነጥለው ይፈላሰፋሉ። እሳት የላሰ ንግግር ያደርጋሉ። ውስብስብ ስብእና አላቸው። በአካልም በመንፈስም የተሞረዱ ናቸው። ሁሉንም እሴቶቻቸውን ተከትለን ብንነጉድ ከምንጩ እንደርሳለን። ልክ እንደ ቅድመ አያቶቻቸው ግሪካውያን ሮማውያንም በጥበብ ድንጋይ ላይ የተመሰረቱ ረዥም ቅጥር ናቸው። ሮማውያኑ ሴኔካ ፣ ማርከስ ኦሬሊየስ ፣ ሁለቱም ፕሊኒ ፣ ሲሴሮ የፍልስፍናም የፖለቲካም ፣ የሳይንስም የጥበብም ሰዎች ነበሩ። መልቲዲሲፕሊናዊ ስብእናዎች በመሆናቸው ሮምን ታላቅ እና የማትነቃነቅ ኢምፓየር አድርገው ለመመስረት አስችሏቸዋል። በሁለት በኩል የተሳሉ ቢላዎች በመሆናቸው ጠንካራ የፖለቲካ አመራር፣ የተሳካ የጦር ሜዳ ገድል፣ የደረጀ መንፈሳዊ ልእልና ነበራቸው።
ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንሻገር። ባቢሎን፣ ሱሜር፣ ሜሶፖቶሚያ፣ ግብፅ፣ እስራኤላውያንን እናገኛለን። ግብፅ ከሮማም ከግሪክም የቀደመች ጥንታዊ የጥቁር አፍሪካውያን ስልጣኔ ናት። ሜሶፖቶሚያ የመጀመሪያውን በታሪክ የተገኘ ስነጽሑፍ የጊልጋሜሽ ኤፒክ(Epic of Gilgamesh) ደራሲዎች ናቸው። ኤፒክ ስነግጥም ሜሶፖታሚያውያን ፈጠሩት ካልን ግሪካውያን በሆሜር የፍፅምና ደረጃ ላይ ሰቅለውታል። ኤፒክ ስነግጥም ለማታውቁት ልብወለድ ባልነበረበት በዚያ የጥንት ዘመን ረዥም ታሪኮችን በግጥም መልክ የሚቀርብበት የስነጽሑፍ ዘውግ ነው። በጣም ቀለል አድርገን ካየነው ልብወለድ በግጥም ልንለው እንችላለን። እንደ ልብወለድ ሴራ ገፀባህሪያት አሉት ግን ከልብወለድ በጣም የሚለይ የረቀቀ የስነጽሑፍ ጥበብ ነው።
ጥቁር ግብጻውያን ለፈርኦኖቻቸው መቀበሪያ ፒራሚዶችን የገነቡ፣ በፓፒረስ ቅጠል ስነፅሁፍን የከተቡ፣ በአስማት ጥበባቸው የታወቁ የራሳቸውን ልዩ ስልጣኔ የፈጠሩ ህዝቦች ነበሩ። ስለ ግብፅ ፈርኦኖች ዘወትር የሚደንቀኝ ጉዳይ አለ። መቃብሮቻቸው ፒራሚድ ከሆነ መኖሪያ ቤተመንግስታቸው እንዴት የላቀ ነበርን?! በእርግጥ ግን ፈርኦኖች ከሞት በኋላ ስላለው ህይወት የበለጠ አትኩሮት የሚሰጡ ፒራሚዶቻቸው ቤተመንግስታቸውን አንበሳ ዶሮን ወደታች እንደ ጫጩት እንደሚገረምም ያሉ ነበሩ። ቴክኒካሊ የግብፅ ፒራሚዶችን የገነቡት እስራኤላውያን ናቸው። መፅሀፍ ቅዱስ የእስራኤላውያን የአእምሮ ጭማቂ ውጤት ነው። የእስራኤላውያን የመንፈስ ልእልና ከስነፅሁፋዊ መፅሀፍ ቅዱስ ይመነጫል። ሰለሞን ትልቁን የኢየሩሳሌም ቤተመንግሥት የገነባው በድንጋይ እና በወርቅ አይደለም―በአምስቱ የሙሴ የህግ መፅሀፍት እንጂ። የሙሴ መፅሀፍት ምህንድስናውን፣ ህክምናውን፣ ኮከብ ቆጠራውን፣ ህግጋቱን ጠቅልለው የያዙ ህዝቦችን በአካልም ሆነ በመንፈስ የመቅረፅ እምቅ አቅም የነበራቸው እና የቀረፁ ጠብሰቅ ያሉ ሰነዶች ነበሩ። የብሉይ ኪዳን ጥበብ እስራኤላውያን በመላው አለም እስከሚበተኑበት ድረስ ትልቅ ህዝብ አድርጓቸዋል። ዳግም ከ70 አመት በፊት እንደ ሃገር ሲመሰረቱ የተአምራዊ ጥንካሬያቸው መፍለቂያ ነበር። በእርግጥ አሁን የግሪክን እና የሮማውያንን አማልክት የሚያመልክ ከመሃከላችን አንድም የለም። የእስራኤላውያን አምላክ ግን ከመቼውም ግዜ በላይ ቢሊየን ተከታዮች አሉት። ይህ የሚያሳየው የእስራኤላውያንን ጂኒየስነት እና ድንቅ የፈጠራ ችሎታ ነው―የፈጠሩት አምላክ የበለጠ ተአማኒ ስነፅሁፋቸውም solid ነው። መፅሀፍ ቅዱስ ሌላ ምንም ሳይሆን የእስራኤላውያን የታሪክ መፅሀፍ ነው―ግማሽ እውን ግማሽ ቅዠት ነው።
እነሆ እስራኤላውያን በመላው አለም ተበተኑ። የሮማውያን ኢምፓየር እና ስልጣኔ ቀስ በቀስ ፈራረሰ። አውሮፓ ከግሪክ የስልጣኔ ማማ ወረደች። መካከለኛው ዘመን ደረስን። ለ400 እና 500 አመት በጨለማ ዳከረች። የቲያትር ቤት ደጃፎች ተዘጉ። አውሮፓውያን በቁስም በመንፈስም ደኸዩ። በመካከለኛው ዘመን የነበረው ብቸኛ የስልጣኔ ጭላንጭል የአረቦች ነው። ነብዩ መሃመድ መፅሀፍ ቅዱስን በራሱ ህዝብ ልክ ሰፍቶ ቅዱስ ቁራንን ፃፈ። የግሪካውያን ጥበብ ወደ አረብኛ ተተረጎመ። በፓይታጎረስ ደረጃ የሚጠሩ የአረብ ሂሳብ ሊቆች ተፈጠሩ። ፊርዳውሲ ሩሚን ካያምን የመሳሰሉ የፔርሺያ ታላላቅ ገጣሚዎች ብቅ ብቅ አሉ። አል ጋዛሊን የመሰለ ፈላስፋ አቪሴናን የመሰለ የህክምና የፍልስፍና እና ሌሎችም የእውቀት መስኮች ሊቅ አቆጠቆጡ ።
በ14ኛው ክፍለዘመን አውሮፓ ድንገት ካንቀላፋችበት ረዥም እንቅልፍ ባነነች። ለ300 አመታት የዘለቀ ተሃድሶ ስታደርግ ፊታውራሪዎቹ ሊዎናርዶ ዳቬንቺ ፣ ሜኬልአንጀሎ እና ሌሎችም ነበሩ። ይህንን ተከትሎ በአውሮፓ የባህል የፖለቲካ የኢኮኖሚ መነቃቃት ተፈጠረ። ከ18ተኛው ክፍለዘመን በኋላ የኢንዱስትሪ አብዮት መቀስቀስ እያንደረደረ ወደ ዘመናዊው አለም ያመጣናል።
ከተሃድሶ ዘመን ተጠቃሽ የስነጽሑፍ ስራዎች መሐል የጣልያናዊው ኤፒክ ገጣሚ ዳንቴ አሊግሄሪ "The Divine Comedy" የሌላኛው ጣልያናዊ የፖለቲካ ፈላስፋ ኒኮሎ ማኪያቬሊ "The Prince" የስፔናዊው ሰርቫንቴስ "ዶን ኪኾቴ" ይገኙበታል። ዮሃንስ ጉተንበርግ የሕትመት ማሽኑን ከፈለሰፈ በኋላ ዘመናዊ ስልጣኔ እየተቀጣጠለ መጣ። መፅሀፍት በብዙዎች እጅ መገኘት ጀመረ። ሳይንስ እና ጥበብ ተስፋፋ። እውቀት የጥቂቶች ጉዳይ ብቻ መሆኑ አበቃ። ወፍራም የለውጥ አየር አሰገመገመ።
እንግሊዝ ነን። አስራስድስተኛው ክፍለዘመን። ንግስቷ ኤልሳቤጥ ናት። ኤልሳቤጥ የሰው ባልን ትታ አገሯን ያገባች የሃገር ፍቅሯ በልቧ ላይ የሚንቦገቦግባት ንግስት ናት። ግዜዋንም ፍቅሯንም ህይወቷንም ለሃገሯ ሰጥታለች። በሷ ዘመን ዊሊያም ሼክስፒር ተወለደ። ሼክስፒር በ52 አመት እድሜው 38 ተውኔቶችን ፃፈ―እያንዳንዳቸው ማስተርፒስ ናቸው። ግማሹ ትራጄዲ ሌሎቹ ኮሜዲ የተቀሩት ደግሞ ታሪካዊ ናቸው። ሼክስፒር ተውኔት በቃኝ ሳይል 154 ሶኔቶች ጽፏል። ሶኔት የግጥም አይነት ናቸው። ታድያ ሼክስፒር የ16ተኛው ክፍለዘመን ብቻ ጠቢብ አይደለም፤ የዘለአለም ነው። የእንግሊዝ ብቻ አይደለም፤ የአለም ነው። ብዙዎቻችን ማክቤዝን ሃምሌትን ሳናነብ ሼክስፒርን በስም ብቻ እናውቀዋለን። አለም ከሱ በፊትም ሆነ በኋላ የሱን ያህል ጥበበኛ አላየችም―ምናልባት ሊዎናርዶ ዳቬንቺን። (ንጉስ ሰለሞን ሌላ አይነት ጥበበኛ ነው) የሼክስፒር ተውኔቶች ለ500 አመታት ቋንቋን ማህበራዊ እሳቤን ስነልቦናን ዘመናዊ ፖለቲካ ላይ ተፅእኖ ፈጥረዋል። ሼክስፒር ብቻውን የጥበብ ቅፅር ነው። እነሆ ከግማሽ ሚሌኒየም(ሺህ―አመት) በፊት የለኮሰው የጥበብ ውጋጋን እስከአሁን ይንቦገቦጋል። እንግሊዝ ለብዙ አመታት አለምን በሥልጣኔ በፖለቲካ በጦር ሃይል መራች። የዛች ሚጢጢ ሃገር ወፍራም ጡንቻዎች ጠቢቦቿ ናቸው። ህዝቦቿን በብርቱ የቀረፁት ገጣሚዎች ፣ ፀሐፊ ተውኔቶች ፣ የልብወለድ ደራሲዎች ናቸው። ከሼክስፒር ቀጥሎ ጆን ሚልተን የእንግሊዝ ትልቁ ገጣሚ ነው። የሼክስፒር ሃገር ልጆች ብርቱ ገጣሚ ናቸው―ቻውሰር፣ ስፔንሰር፣ ቴኒሰን፣ ኮልሪጅ፣ ሼሊ፣ ባይረን፣ ብሌክ፣ ዎርድስዎርዝ። የተውኔት ደራሲዎችም አሉ―ሚድልተን፣ ቤን ጆንሰን፣ ማርሎው። ከእንግሊዝ ፈቀቅ ስንል በመላው አውሮፓ በተለይ ፈረንሳይ ጀርመን ታላላቅ ፀሐፊ ተውኔቶች ነበሩ።
ቪክቶሪያ ዘመን ላይ ስንደርስ የተውኔት እና ግጥም ተወዳጅነት እና ጉልበት ቀንሷል። ዘመኑ የልብወለድ ነው። ታላቁ የልብወለድ ደራሲ ደግሞ ቻርልስ ዲክንስ። ዘመኑ አስራዘጠነኛው ክፍለ ዘመን። የኢንዱስትሪ አብዮት በመፈንዳቱ እልፍ ፋብሪካዎች ተከፍተዋል። ዲክንስ ራሱ በልጅነቱ የፋብሪካ ሰራተኛ ነበር። ይህንኑ ገጠመኙን በ"Hard Times" ልብወለድ መፅሀፍ አድርጎታል። በዘመኑ መፅሀፍት የሚወጡት በአንድ ቅፅ ተጠርዘው አይደሉም። በየሳምንቱ በሚወጡት ጋዜጦች እንጂ። አንድ ጋዜጣ ማለት አንድ ምእራፍ ነው። የሚቀጥለውን ምእራፍ ለማንበብ ሌላ አንድ ሳምንት መጠበቅ ግድ ነው። የልብወለዶች ተወዳጅነት የጋዜጣ ሽያጩን አደራው።( እዚህ እኛ ሃገር አዲስ አድማስ ይህንን ቅርፅ ሞክሮታል። አራት አብነቶችን አስታውሳለሁ። እነዚህ መፅሀፍት በአንድ ተጠርዘው ከመውጣታቸው በፊት በየሳምንቱ ቅዳሜ አዲስ አድማስ ላይ አንብበናቸዋል―የኦዶኒስ "የአና ማስታወሻ" ትርጉም፣ የራሱ የነብይ መኮንን "የኛ ሰው በአሜሪካ"፣ "የፍሬሿ ማስታወሻ(የፀሀፊዋ ስም ሄርሜላ መሰለኝ)፣ የአብርሃም ረታ አለሙ "አልን አስባልን ተባለ") ይቺ በየሳምንቱ እየከፋፈሉ ልብወለድን መዘርዘር መለኛ ሳይሆን አይቀርም። አንባቢዎች ያነበቡትን ለማመንዠክ አንድ ሙሉ ሳምንት አላቸው። የሚቀጥለውን ክፍል የሚጠብቁት በጉጉት ነው። ደረስኩ ሲልም የሚነበበው በከፍተኛ ሃይል ነው። መጽሐፉን ማንበብ እንዲያው የመጨረስ ጉዳይ ሳይሆን የስሜት ጉዳይ ይሆናል። እንደገና እንግሊዝ ነን። በቪክቶሪያ ዘመን የፈሉትን የልብወለድ ደራሲዎች ለመዘርዘር እዚህ ጋር ቦታ አይበቃም። እንግሊዝ በዚህ ሁሉ የጥበብ አጀብ በአለም ላይ ብርቱ ሃይል ሆነች። የዜጎቿ ንቃተህሊና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ። እንግሊዝነት የነቄነት የአዋቂነት የብልጥነት የገዛ ጥቅም አስጠባቂነት አለም አቀፍ መለያ ሆነ። ሶስት አራተኛው አለም የእንግሊዝ ግዛት ሆነ። ታድያ ይህ እንግሊዛውያን ጥሩ አልሞ ተኳሾች ስለሆኑ ብቻ አይደለም―ከኋላ ያለው የጥበብ፣ የእውቀት፣ የንቃት ደጀን ነው። ይህንን የሚቀርፁት ደግሞ ደራሲዎች፣ ፈላስፋዎች፣ ገጣሚዎች፣ አሳቢዎች ናቸው።
ሃያኛው ክፍለዘመን ላይ ደረስን። የአለም ሁኔታዎች ተቀያይረዋል። ሃያኛው ክፍለዘመን የከፍታም የዝቅታም ዘመን ነው። ሳይንስ ከፍተኛ እምርታ ያሳየበት ዘመን ነው። ሁለት የአለም ጦርነቶች በማድረግ የሰው ልጅ መንፈስ የዘቀጠበት ዘመን ነው። አልበርት አንስታይን ፊዚክስን ሪቮሊዩሽናይዝ ያደረገበት ዘመን ነው። ሂትለር ስድስት ሚሊየን አይሁዳውያንን የፈጀበት ዘመን ነው። ካርል ማርክስ በታላቅ ፍልስፍናው አለምን በሁለት ታላላቅ ጎራ የከፈለበት ዘመን ነው። ስታሊን የማርክስን ፍልስፍና በተሳሳተ መንገድ ተረድቶ 50 ሚሊየን ራሽያውያንን እንደ እባብ የጨፈጨፈበት እንደ ውሻ የቀጠቀጠበት ዘመን ነው። ፍሩይድ ስነልቦናዊ እሳቤን የሕይወት ማጠንጠኛ አድርጎ ማእከላዊ መሰረታዊ ጥያቄ የጠየቀበት ዘመን ነው። ማኦ―ሴ―ቱንግ(ማኦዜዱንግ) 78 ሚሊየን ቻይናውያንን ወደ ሞት የሸኘበት ዘመን ነው። በአጠቃላይ ቻርልስ ዲክንስ በ"የሁለት ከተሞች ወግ" ውስጥ እንዳለው "ዘመኑ ተቃራኒ ሁኔታዎች የነገሱበት ዘመን ነበር" ሰዎች በቀኝ በኩል አስደናቂ ስልጣኔ ይገነባሉ። በግራ በኩል ተሰምቶ የማይታወቅ ለአይንና ለጆሮ የሚቀፍ ተወዳዳሪ የሌለው የጭካኔ እልቂት ይፈፅማሉ። የሰዎች መንፈስ በሁለት አፅናፎች በከፍታ እና ዝቅታ በልእልና እና ድድብና መካከል እንደ ሸማኔ ድር የሚመላለስ ድውር ነው። ጥበብ አሁንም አለምን መምራት አላቋረጠችም። መልኳን ቀየረች እንጂ። ሳይንሳዊ ስልጣኔው ብዙ ነገሮችን ሪቮሊዩሽናይዝ አደረገ። ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ተፈለሰፈ። ሲኒማ ተፈጠረ። ሰዎች ጥበብን የሚያስተላልፉበትና የሚቀበሉበት መንገድ ሙሉ ለሙሉ ተቀየረ። እንግሊዝ አለምን በስውርም ሆነ በገሃድ የምትመራበት በትረ―ስልጣኑን ለሰሜን አሜሪካ አስረከበች። ሆሊውድ የአለም የጥበብ ማእከልና መለኪያ ሆነ። ከገዛ ፈሳችን ቀድሞ ሆሊውድ ያስነጠሰው ይደርሰናል። መፅሀፍት ወደ ፊልም ይቀየራሉ፤ በቴሌቪዥን ይታያሉ፤ በሬዲዮ ይተረካሉ። ነገሮች መልቲሚድያ ሆኑ። ብሮድዌይ የአለም የቲያትር ማእከል ሆነ። የአሜሪካ የመካላከያ የኢኮኖሚ የፖለቲካ የበላይነት ሁሉ እጁን ይዞ የሚመራው ፊታውራሪ ሆሊውድ ነው። አሜሪካ ውስጥ ትልቅ ቀውስ ሲፈጠር የሆሊውድ ፕሮዲዩሰሮች ኋይትሃውስ ይጋበዛሉ። መመሪያ ይቀበላሉ። ቢሊዮን ዶላር ይመድባሉ። በማር የተለወሰ ፖሊሲያቸውን በፊልም ያሽጋሉ። እኛም ሲኒማ ቤት ደጃፍ እንሰለፋለን። በገዛ ገንዘባችን መዝናኛ ገዝተን እራሳችንን እንሸጣለን። በአራት ሜትር አቡጀዲ ያየነውን ትእይንት የመጨረሻ እውነት አድርገን እንቀበላለን። አሜሪካንን ሊያናውጣት ያሰፈሰፈው ወጀብ ከሽፎ ወደ በለጠ ከፍታ ትስፈነጠራለች። ፊልሞች የመጨረሻው የእውቀት ምንጭ ሆኑ።
21ኛው ክፍለዘመን ከገባ እነሆ 20 አመት ሞላው። አሁንም ጥበብ ሰዎች ጋር የሚደርስበት መንገድ መልኩን ቀየረ። ሰዎች በኪሳቸው የሚያስቀምጡት በእጃቸው የሚይዙት ትንንሽ ሃይለኛ መሳሪያዎች ተፈለሰፉ። እንደ በፊቱ ጥበብን ለመቋደስ ቦታን ግዜን መጠበቅ ቀረ። ሰዎች በማንኛውም ሁኔታ የሚፈልጉትን መረጃ፣ እውቀት የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጠረ። ነገር ግን የዘመኑ ቴክኖሎጂ የዘመኑን ተግዳሮት ፈጠረ። ጥበብ በብዛት ስትተኮስ በጥራት ተዘረረች። ጥልቀት አጣች። በየቦታው መገኘቷ አረከሳት። በብልጭልጭ ተጀቡና እውነተኛ ውበቷን አጣች። ለሃያ እና ሃያ አንደኛው ክፍለዘመን የአውሮፓ መልስ እግርኳስ ነበር። በስነፅሁፍ ያጡትን ከፍታ በሌላ ጥበብ ለመመለስ ኳተኑ። ይሁን እንጂ ተከታይ እንጂ ቀዳሚ መሆን አልቻሉም። እግርኳስ ጥልቀት ያለው ጥበብ አይደለም።
የትም የአለም ጫፍ ሂዱ። ስልጣኔ ባበበበት ሁሉ የጥበብ ችግኝ አለ። ጥበብ ስልጣኔን ይወልዳል ። ስልጣኔ መልሶ የበለጠ ጥበብን ያበረክታል። ሁለቱ አይነጣጠሉም። ታላቅ የስነጽሑፍ ስራ ያልፈጠረው ያልኮተኮተው ያላጀበው ስልጣኔ ኖሮ አያውቅም።
ይሄንን ሁሉ ይዘን ወደ ኢትዮጵያ እንምጣ። በተለምዶ ኢትዮጵያ የ3000 አመት ታሪክ ባለቤት የአክሱም ስልጣኔ መስራች የሚለው ሃሳብ ከሁሉም ገንኖ ይሰማል። አንዳንዶች የኢትዮጵያን የጽሑፍ ታሪክ እስከ 5,500 አመት ያደርሱታል። ሄኖክ ኢትዮጵያዊ ነው፤ የኖህ ቅድመ አያት ነው፤ የአዳምና ሄዋን ገነት ግዮን ወንዝ አጠገብ ኢትዮጵያ መሐል ነው ይላሉ። ይህንን ሁሉ መረጃ ተከትላችሁ ብትነጉዱ አሁንም ምንጩ ጥበብ ነው። ኢትዮጵያ የሶስት ሺህ አመት ቱባ ታሪክ ባለቤት የሚለው ተረክ የመጣው ከሌላ ከምንም ሳይሆን የጥንት አባቶቻችን "ክብረ―ነገሥት" ፣ "ፍትሐ―ነገሥት" እና "አውደ―ነገሥት"ን ፅፈው ስላስቀመጡልን ነው። ወደ 5,500 አመት የተለጠጠው ደግሞ በመፅሀፈ ሄኖክ ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ረዥም ታሪኳ ሌሎች ብዙ ስልጣኔዎችን አስተናግዳለች። ታድያ ሁሉም ስልጣኔዎች የጥበብ ምልክት ትተው አልፈዋል―የአክሱም ሃውልት፣ የላሊበላ ቤተክርስቲያን፣ የፋሲል ግንብ እና ሌሎችም ብዙ።
(ምስሉ፣ ጣሊያናዊው ራፋኤል በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የሳለው "The School of Athens " የተሰኘ ዝነኛ ስእል ነው። ስእሉ በጥንታዊ ግሪክ የነበረውን የዘመኑን የፍልስፍና መንፈስ ጠቅሎ ይዞ የሚያሳይ የራፋኤል ታላቁ ስራ ነው።
በስእሉ መሐል ላይ የሚታዩት አበይት የግሪክ ፈላስፋዎች ፣ እንዲሁም የስእሉ ማእከላዊ አትኩሮቶች፣ በግራ ፕሌቶ( አፍላጦን) እና በቀኝ ተማሪው አሪስቶትል (አሪስጣጣሊስ) ናቸው። ሁለቱም በግዜው ዘመናዊ የሚባሉ መፅሀፍትን በግራ እጃቸው ይዘዋል። ወደ ሀሳባዊነት / idealistic ፍልስፍና የሚያዘነብለው አፍላጦን እጁን ወደ ላይ ጠቁሞ ይታያል። በተፃራሪ በተግባር የተፈተነ/empiricism ፍልስፍና የሚማርከው ወጣቱ አሪስጣጣሊስ ፣ እጁን ወደ ምድር ጠቁሞ ይታያል።
በተጨማሪም እውነት እና እውቀትን የሚያጠና የፍልስፍና ዘርፍ/metaphysics ተከታዮች በአፍላጦን በኩል ሲሆኑ ቁስ አካልን የሚያጠኑ / physics ደግሞ በአሪስጣጣሊስ በኩል ተሰብስበዋል።
በስእሉ ላይ ከተካተቱት ሌሎች ፈላስፋዎች እና ሌሎችም አብይ የታሪክ ፣ የስነ ጥበብ እና የሳይንስ ሰብእናዎች መሐል ሶቅራጥስ ፣ ዲዎጋን ፣ ኤፒኩረስ፣ ፓይታጎረስ ፣ ኢኩሊድ፣ አርኪሜደስ ፣ አናክሲማንደር ፣ ዜኖ፣ ፕሊቲነስ፣ ሚኬልአንጀሎ፣ ሊዎናርዶ ዳ ቪንቺ ፣ ትልቁ እስክንድር ፣ እንዲሁም ሰአሊው እራሱ ራፋኤል ይገኙበታል።
© Tewodros Shewangizaw