05/12/2025
አንድ ጊዜ አንድ ባልና ሚስት ወደ ባንክ በመሄድ ላይ ሳሉ፣ በአንድ ጥግ ላይ ምግብ በመስረቁ ምክንያት በሰዎች ተደብድቦ የወደቀ ህፃን ተመለከቱ። ሰውነቱ ቆስሎና ደክሞ ያዩት ይህ ህፃን አንጀታቸውን በላው።
በሁኔታው በጣም ስለደነገጡ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ወሰዱት። የህክምና ወጪውንም ሙሉ ለሙሉ ከፍለው፣ ህፃኑን ወደ ቤታቸው በመውሰድ ተንከባከቡት። "ሉክ" የተባለው ይህ ህፃን ከህመሙ አገግሞ ሲነቃ የልቡን እውነት አወጣላቸው። በሚንቀጠቀጥና ዝቅተኛ ድምፅ፣ "ሁሌም ዶክተር መሆን ነበር ህልሜ፤ ነገር ግን ወላጆቼ በመኪና አደጋ ከሞቱ በኋላ ጎዳና ላይ ወደቅሁ። ህይወቴን ለማትረፍ ስል ምግብ ለመስረቅ ተገደድኩ" አላቸው። ባልና ሚስቱም በልጁ ታሪክ ልባቸው ተነካ፤ እንደ ልጃቸው አድርገው ሊያሳድጉትና ሊያስተምሩት ወሰኑ።
ነገር ግን ነገሮች እነሱ እንዳሰቡት አልሆኑም። የገዛ ልጃቸው ወላጆቹ ለሉክ በሚያሳዩት ፍቅርና እንክብካቤ በቅናት እሳት ተቃጠለ። አንድ ቀን ወላጆቹን አስጠራና፣ "ይህን የጎዳና ልጅ እዚህ ቤት ካስቀራችሁት ራሴን አጠፋለሁ! ወይ እኔን ምረጡ ወይም እሱን!" ሲል አስፈራራቸው።
ባልና ሚስቱ በህይወታቸው ገጥሟቸው የማያውቅ ከባድ ፈተና ውስጥ ወደቁ። የገዛ ልጃቸው ህይወት አደጋ ውስጥ እንዳይገባ በመስጋት፣ የማይቻል የሚመስል ውሳኔ ወሰኑ። ሉክን ጠሩትና የነበራቸውን ጥሪትና የቆጠቡትን ገንዘብ ሰጥተው፣ አይኖቻቸው በእንባ እየረጠበ መረቁት። ሉክም ውለታቸውን አስቦ፣ እያዘነ ተሰናበታቸው።
ከዚያ ጊዜ በኋላ አስር አመታት አለፉ። የተምበሸበሸው ልጃቸው ግን እንደጠበቁት አልሆነም። ምግባረ ብልሹ፣ ሱሰኛና ቁማርተኛ ሆነ። ወላጆቹ ከእሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥ ሲፈልጉ፣ ይባስ ብሎ ያለችቸውን ቤት ሽጦ ከገዛ ቤታቸው አባረራቸው። እነዚያ አዛውንቶችም ሜዳ ላይ ቀሩ።
አንድ ቀን አዛውንቱ ሰውዬ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ፕላስቲክ ሲለቅሙ፣ በከፍተኛ ፍጥነት ይጓዝ የነበረ መኪና ገጫቸው። በሰዎች እርዳታ ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም ሁኔታቸው አሳሳቢ ነበር። ዶክተሩ ወደ ሚስትየው መጣና፣ "ባለቤትዎ አስቸኳይ ቀዶ ጥገና ያስፈልገዋል፤ አለበለዚያ ህይወታቸው ያልፋል። ነገር ግን መጀመሪያ ክፍያ መፈጸም አለባችሁ" አላቸው።
ሚስትየው ተስፋ በቆረጠ ስሜት አለቀሰች። "ምንም የለንም፤ የሚረዳንም ሰው የለም፣ እባካችሁ!" እያለች ተንሰፈሰፈች።
በዚያው ቅፅበት አንዲት ነርስ አንድ ፖስታ ይዛ መጣች። "ዶክተሩ ይህንን እንድሰጥዎት ነግሮኛል" አለቻት። ሚስትየው ፖስታውን ተቀበለች፤ ፖስታው ላይ "ለእማማ" የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል።
"እማማ? አይሆንም... የኔ ልጅ ጨካኝ ነው፤ እሱ ዶክተር ሊሆን አይችልም፣ ማን ሊሆን ይችላል?" ስትል በሀሳብ ተዋጠች። እየተንቀጠቀጡ ባሉ ጣቶቿ ደብዳቤውን ከፈተችው። ቃላቶቹን ስታነብ ግን በድንጋጤ ደርቃ ቀረች። ደብዳቤው እንዲህ ይላል፡-
"እኔ ነኝ፣ ሉክ። ከአስር አመት በፊት ያዳናችሁኝ ያ ቤት አልባ ልጅ። ዛሬ የዚህ ሆስፒታል ዋና ሃላፊ ዶክተር እኔ ነኝ። የአባዬን ቀዶ ጥገና ክፍያ ሙሉ ለሙሉ ከፍያለሁ፤ አባዬ በጥሩ እጆች ላይ ነው ያለውና አትስጉ። እንዲሁም አንድ ቀን ፈጣሪ ያገናኘናል በሚል ተስፋ ለሁለታችሁ የሚሆን ቤት ገዝቼ አስቀምጫለሁ። እባካችሁ ወደ ቤታችሁ ኑ።"
ሚስትየው የደብዳቤውን መልእክት ስትጨርስ ከንፈሮቿ ተንቀጠቀጡ። የአስር አመት የናፍቆት፣ የህመም እና የሃዘን ስሜቷ በደስታ እንባ ታጥቦ ጠፋ።
.... ......... ..........
ደግነት የዘራነው ዘር ነው። ዛሬ መልካም ብናደርግ፣ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ እጥፍ ሆኖ ወደ እኛ ይመለሳል።
# በጎነት አይከሽፍም!