14/03/2024
Shiferaw
ከልብ የመነጨ ይቅርታን እጠይቃለሁ።
በትግራይ ጦርነት ወቅት ከወ*ያኔ እንቅስቃሴና ግብ አንፃር ይዤ
የነበረው አቋም ትክክለኛ እንደነበር አልጠራጠርም። ለጦርነቱ ወ*ያኔ የነበረውን ወሳኝ ሚናም በማለባበስ ተጠያቂነቱን ከወ*ያኔ ላይ ለማውረድ የሚደረገው ጥረትም ነጭ ውሸት ስለሆን አልቀበለውም።
ከዚህ አንፃር በጦርነቱ ወቅት ይዤ የነበረው አቋምና የአቅሜን ያህል ያደረግሁትም ድጋፍ ተገቢ ነበር ብዬ አምናለሁ።
በሌላ በኩል ደግሞ ትልቅ ፣ በጣም ትልቅ ስህተት መሳሳቴን ተረድቻለሁ ፤ በዚህም ልቤ በፀፀት አለንጋ ይገረፋል።
ይኸውም ፥ ጦርነቱ ከተጀመረ ጥቂት ሳምንታት አንስቶ በትግራይ ንፀሃን ላይ እየደረሰ ነው ይባሉ የነበሩ የጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የምግብ አቅርቦት እገታ፣ የዘፈቀደ እስርና እንግልት ወዘተ ሁሉ በወ*ያኔ እና በፕሮፓጋንዳ ሰራዊቱ የሚነዛ የሀሰት ክስ ይመስለኝ ነበር። ይህ እንዲመስለኝ ደግሞ ከወ*ያኔ ተመሳሳይ ባህሪ አንስቶ በርካታ ሌሎች አሳሳች ምክንያቶችም ሚና ነበራቸው። በርግጥ በወ*ያኔ የእስስትነትና ጨካኝነት ሆን ተብለው የተፈጠሩ ሴራዎች እንደነበሩም እውነት ነው። ይሁንና ከዚህ ባሻገር በርግጥም ንፁሃን በተጠቀሱት መልኩ የበርካታ ግፎች ሰለባ እንደነበሩ ከተረዳሁ ወራት ተቆጥረዋል። በዚህም የተነሳ ፥ በንፁሃን ላይ ይደርስ የነበረን ግፍ እውነትነቱን ለማረጋገጥ በቂ ጥረት ሳላደርግ በመቅረቴ ጆሮ ዳባ ልበስ ላልኩት በደል፣ ተፈፅመው ሳለ እንዳልተፈፀሙ እርግጠኛ ሆኜ የማይገባ ሚና በመጫወቴ ልቤ እጅግ፣ እጅግ ያዝናል።
ከክፉ መንፈስ ባልነሳም ፥ ለዚህ ያልተገባ ሚናዬና የንፁሃንን ህመም ያልተጋራሁ በመሆኔ እጅግ ከባድ ስህተት ሰርቼ ነበርና በዚህ በጣም አዝናለሁ ፤ በፀፀት ከተሞላ ልብ በመነጨም ለዚህ ተግባሬ ይቅርታን እጠይቃለሁ።