20/07/2022
ጋሽ ፀጋዬ፣ አፍሪካ እና አፍሪካዊነት
በአፀደ ምስጋናው
የተለያዩ ፀሐፍትን ስራዎች ለተለያዩ አላማዎች ስንል እናገላብጣለን፡፡ በተለይ የታላላቅ ሰዎችን ስራ ከመዝናኛነቱ በተሻገረ መልኩ የአፃፃፍ ቴክኒካቸው ማርኮን፤ ምክንያታዊ እሳቤአቸውን በማድነቅ ወዘተ ከመጽሐፍቶቻቸው ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንፈጥራለን።
በመጽሐፎቻቸው የሚሰጡንን ፍልስፍናቸውን ለመቃረም የምንተጋላቸው ላቅ ያሉ ፀሐፍትም አሉ፡፡ ፍዮዶር ዶስቶቪስኪ፣ ፍሬድሪክ ኒቼ፣ አልበርት ካሙ እና አየን ራንድን የመሳሰሉ ስሞች በስነ ጽሑፍ ስራዎቻቸው የምንደመምባቸውን ያህል በስነ ጽሑፎቻቸው አሾልከው የሰጡን ፍልስፍናቸው ገዝፎ ሲያመራምረን እና ሲያሟግተን ይኖራል።
በእኛም ሀገር እንደ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን፣ መንግስቱ ለማ፣ ሰለሞን ደሬሳ፣ በዓሉ ግርማ፣ ስብሃት ገብረእግዚያብሔር፣ አቤ ጉበኛ፣ ባሴ ሀብቴ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ተስፋዬ ገሰሰ፣ መስፍን ሀብተማርያም፣ ደምሴ ጽጌ፣ ሙሉጌታ ተስፋዬ እና ሌሎች የሥነ ጽሑፍ ባለ መክሊቶች በተሰፈረላቸው የእድሜ መጠን ልክ አንቱ የሚያስብላቸውን ስራ ሰርተው ያለፉ ናቸው፡፡
በሥነ ጽሁፎቻቸው የሚያነሷቸው የህይወት ስንክሳሮች የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ከማሳየት ባለፈ አዘቦታዊነትን ተሻግረው የሚሄዱ በፀሐፊዎቹ ፍልስፍናዊ ሀሳቦች የተዋቡ ሆነው እናገኛቸዋለን።
‹‹እስኪ የእገሌን ፍልስፍና ላንብብ›› ብለን ባንጀምረውም የሥነ ጽሑፍ ጥማታችንን ለማብረድ የከፈትነው መጽሐፍቶቻቸው የፀሐፍያኑን ፍልስፍና ይግቱናል ወይም እንዲያ እንዲሰማን ተደርገው ተከትበዋል።
በዚህም ምክንያት ሥነ ጽሁፎቻቸው ከትልልቅ የትምህርት ማዕከላት፣ ቤተ መዛግብት እና ከተመራማሪዎች መጸሀፍት መደርደሪያ (shelf) የማይጠፉ ሆነዋል፡፡ ዛሬም ይጠናሉ፣ ይመረመራሉ፣ ‹‹እንዲህ ሊሉ ነው፤ የለም! እንዲያ ማለት ፈልገው ነው›› ይባልላቸዋል፡፡
በዚህ ወጋችን የታላቁን የሥነ ጽሁፍ ሊቅ የሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህንን ሥራዎች መነሻ በማድረግ በአፍሪካ እና አፍሪካዊነት ላይ የፀሐፊው ፍልስፍና ምን ይመስል እንደነበር ለማየት እንሞክራለን፡፡
ሚካኤል ሽፈራው “ሀሁፐፑ” የሚለውን የጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህንን ቴአትር መነሻ በማድረግ ‹‹ምስጢረኛው ባለቅኔ›› የሚል መጽሐፍ ጽፏል፡፡
ኤርምያስ ሁሴን ጋሽ ፀጋዬ በተለያየ ጊዜ የተናገራቸውን፣ የፃፋቸውን እና ስለሱ የተነገሩ ጉዳዮችን በማሰባሰብ ‹‹እሳት እና ውሃ›› በሚል መጽሐፍ አሳትሟል፡፡
የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ስራውን ወደ መጽሀፍ በመቀየር ‹‹የፀጋዬ ገብረ መድህን ሥራዎችና ፍልስፍና›› በሚል በቅርቡ ለአንባቢያን ያደረሰው ደሳለኝ ስዩም፤ በፀጋዬ የሥነ ጽሁፍ ሥራዎች ሴቶች የተወከሉበትን አግባብ በመተንተን ሎሬቱ ስለ ሴቶች የነበረውን ፍልስፍና ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡
እነዚህ ጸሐፍያን የፀጋዬ ስራ ግድ ሰጥቷቸው በመጽሐፍ መልክ ለአንባብያን ማድረሳቸው የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም በታላቁ ሰው ፍልስፍና ላይ የተሰሩ ስራዎች ግን በቂ አይደሉም። በእርግጥ በተለያዩ መድረኮች ላይ ቴዎድሮስ ገብሬን የመሳሰሉ ታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች የፀጋዬን የስነ ጽሑፍ ሥራዎች ከሀገር ግንባታ አንፃር የተነተኑበት ሁኔታ እንደነበር ልብ ይሏል።
ከዚህ ባሻገር ጋሽ ፀጋዬ በጠጣር፣ ጭፍግ እና የተወሳሰቡ የሞራል ጥያቄዎች የሸመናቸውን የስነ ጽሑፍ ስራዎች በፍልስፍና አይን ሊመረምሩለት የደፈሩ ኢትዮጵያዊ የሥነ ፅሁፍ ሰዎችን ለመቁጠር መነሳቱ የሚያወላዳ አይደለም፤ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ አፍሪካዊ እሳቤውን ለማየት እንሞክራለን ስንል ከትህትና በተሻገረ ላለመቻል በቀረበ ሁኔታ መሆኑን ልብ እንበል፡፡
ይልቅ በእግረ መንገዳችን እንደሚቀርብብን ሀሜት ሳይሆን የጥበብ ሰዎቻችን ስለ አፍሪካ የሚገድዳቸው እንደሆኑ ለማየት ይረዳናል፡፡ የራሱ የፀጋዬን ሥራ በፍልስፍና መነጽር የሚመረምሩ የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን እንደምንሻ ጥቁምታ መስጠትም ያሻል፡፡
ፀጋዬ ‹‹Black Antigone›› ‹‹The epic of ezop›› እና ‹‹Prologue to African Conscience›› የሚሉ የሥነ ጽሑፍ ስራዎቹ ስለ አፍሪካዊነት ያለውን ምልከታ ያሳየባቸው ናቸው። ‹‹Proud to be African›› የሚለው ሥራው እ.አ.አ በ2002 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት መዝሙር እንዲሆን ተመርጧል።
በእነዚህ ሥራዎቹ የዓለም ስልጣኔ ከአውሮፓዊቷ ግሪክ ይጀምራል የሚለውን የበርካቶች ሀሳብ በመገልበጥ የግሪኩን ጨምሮ የዓለም ስልጣኔ የሚጀምረው ከአፍሪካ እንደሆነ አሳይቷል፡፡ ‹‹ስለ ስልጣኔ አውሮፓ እና አሜሪካ ምን አግብቷቸው ያወራሉ›› የሚለው ፀጋዬ የአውሮፓ ስልጣኔ የሮም እንደሆነ፤ ሮም ደግሞ ሥልጣኔዋን የቀዳችው ከግሪክ መሆኑን እና ግሪክ በአንፃሩ የአክሱምን ስልጣኔ እንደያዘች ያስረዳናል፡፡ ይህም የሆነው የሰው ዘር በዓለም በሙሉ የተበተነው ከዚሁ ከዓባይ ዳርቻ በመሆኑ የሥልጣኔ ምንጮቹ እኛ ነን በማለት ነው።
በእነዚህ ሥራዎቹ ውስጥ ለሚያነሳቸው ሙግቶች አስረጅ በማድረግ አርኪዮሎጂስቶችን ያነሳና የሰው ልጅ እዚህ እንደ ተፈጠረ ከተስማማን ዘንዳ ፈጠራም የጀመረው እዚሁ ነው፤ እኛም የአባቶቻችን የፈጠራ ውጤት ተረካቢዎች ነን ይላል፡፡
የነገሮች አፈፃፀም ወደ ጅማሪያቸው እንደሚያመራ፤ የትኛውም የዓለም አጽናፍ ሥልጣኔ በእሽክርክሪት ውስጥ ዙሮ ምንጩን የሚያገኘው ከወደ አፍሪካ መሆኑን በመሞገት የሥልጣኔ ብርሀን መፍለቂያዎቹ እኛ እንደሆንን ያስረዳል፡፡
‹‹… Who walked first in the footprint of the gods?
Across the sacred mountain of Cush*tic cam
He is the first born of earth and sky mother Atbara
Her lightning throne was sent down for him from the cosmos …››
እንኳን የዚያን ክቡድ ሰው ቅኔ ቀርቶ የትኛው ግጥም ያለባለቤቱ የማይነድ ቢሆንም፤ ወጋችንን ያዋዛልን ዘንድ በነፃ ትርጉም ወደ አማርኛ መንዝረን ስናየው በተቀራረበ መንፈስ ጋሽ ፀጋዬ በኤዞፕ ግጥሙ እንዲህ ይለናል፡-
‹‹ከሁሉ አስቀድሞ፤ በፈጣሪ ፈለግ ማን ነው የተራመደ?
በኩሽ ካም ተራራ፤ በተቀደሰው መስክ ሄዶ የነጎደ፡፡
የእናቱ አትባራ የዘር ሀረግ ትውልድ፤ የምድር ሰማይ በኩር፣
መመረጥ ያገኘ፤ ከላይ የተላከለት የብርሀን ዙፋን ምክር፡፡››
እውነትን ማወቅ ነፃ ያወጣል የሚለው ፀጋዬ፤ የዓለም ህዝብ ማንነቱን አያውቀውም ወይም አውቆ ዘንግቶታል፤ የሁላችንም ቤት አፍሪካ ናት ይላል።
የዓለም ስልጣኔ ያበበው የአባይን ምንጭ ተከትሎ መሆኑን በማስገንዘብ አፍሪካ የመጀመሪያ ፍጡር የፈጣሪውን ዱካ ተከትሎ የተራመደባት የተቀደሰች ምድር መሆኗን በሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹ አሳይቶናል፡፡
እንደ አብዛኞቹ ፀሀፍት እንደ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ሀዘን እና ደስታ አይነት ስሜታዊ ሀሳቦች ላይ ብቻ ተመርኩዞ የማይፅፈው ፀጋዬ፤ አፍሪካዊነትን የሥነ ፍጥረት መነሻ አድርጎ ያየዋል፡፡ አፍሪካዊነትን ባገነኑት ስራዎቹ አፍሪካዊነት ተፈጥሮ፣ ባህል፣ እምነት እና ታሪክ በተባሉ ሀሳቦች ውስጥ የሚደረስበት እውነት እንደሆነ አንፀባርቋል።
የአፍሪካውያንን ንቃት ሰብኳል፤ ወደ ራሳችን መለስ ብለን እንድናይ በማስገንዘብ የነገሮች ጀማሪ መሆናችንን እና የሰው ልጅ የቱንም ያህል የረቀቀ የሥልጣኔ ርምጃ ውስጥ ቢገባ ጅማሮው እዚህ አፍሪካችን ውስጥ እንደሆነ መዘንጋት እንደሌለበት ያሳስባል፡፡ በመሆኑም በመንፈስ ከአፍሪካዊነታችን ርቀን መሄድ እንደማይኖርብን አሳስቦናል፡፡
የሰው ልጅ የቱንም ያህል በአካላዊ ባርነት ውስጥ ቢማቅቅ የመንፈሱን ጥንካሬ እስካልተነጠቀ ድረስ ነፃ ነው፤ አዕምሮው እና መንፈሱ ባሪያ የሆነ እንደሆነ ያን ጊዜ ወየው ይበል፡፡ የአዕምሮ እና የመንፈስ ነፃነትን የሚጎናጸፈው ደግሞ ማንነቱን በብርቱ የፈለገ እንደሆነ ነው ይለናል፡፡
በፀጋዬ እምነት አፍሪካውያን ግራ ቀኝ መመልከታችንን በመግታት ወደ ውስጥ መመልከት መጀመር ይኖርብናል፡፡
‹‹Prologue to African Conscience›› በሚለው ሥራው አፍሪካውያን የህሊና ነፃነታቸውን እንዲያስጠብቁ፤ የኋላ ታሪካቸውን እንዲመረምሩ፣ ባህል እና እምነታቸውን እንዲያስጠብቁ ይመክራል።
‹‹ … It looks right
It looks left
It forgets to look into its own self:
The broken yoke threatens to return
Only, this time
In the luring shape
Of luxury and golden chains
That frees the body
And enslaves the mind… ››
‹‹… ወደ ግራ ወደ ቀኝ በመዋተት፤
ወደ ራስ መመልከትን እየረሱ፡፡
አውልቀው የጣሉትን፤
የወደቀን ቀንበር መልሶ ማንገሱ፡፡
ይሄኔ ነው እንጂ …
በወርቅ ሰንሰለት ቅንጦት ሲታለሉ፤
በአካል ነፃ ሆነው፤
የገዛ አዕምሯቸውን ለባርነት መጣሉ፡፡››
የፀጋዬ ሥራዎች የሀገር ፍቅር፣ አንድነት፣ እንግዳ ተቀባይነት እና ነፃነት እና አትንኩኝ ባይነት ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጡ እሴቶች እስኪመስሉ ድረስ የተሰራንባቸው ንጥረ ነገሮች መሆናቸውን ይነግረናል፡፡
በአቡነ ጴጥሮስ በኩል የተገለፀውን የሀገር ፍቅር፣ ለሀገር አንድነት የተዋደቀውን የመቅደላውን ቴዎድሮስ እና ለሉዓላዊነት ተጋድሎ ትዕምርት የሆነውን የአድዋ ጦርነት በዋና ታሪካዊ ክስተትነት እየመዘዘ ኢትዮጵያውያንን በጋራ ፈትለው ያቆሟቸውን እውነቶች ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍናው ማንፀሪያ አድርጓቸዋል።
ይሄንኑ እውነት ይዞ ኢትዮጵያዊነትን ሰበዝ እና አለላ በማድረግ፤ አፍሪካዊነትን ሰፍቶ ለማሳየት ይሞክራል፡፡
በፀጋዬ ህልፈት ማግስት ስለፀጋዬ የፃፉት ሪቻርድ ፓንክረስት ይህን እውነት ሲያስረዱ ኢትዮጵያውያን ማንም የማይጋራቸው የብቻቸው የሆነ ጠንካራ እሴት ያላቸው ህዝቦች ቢሆኑም በኢትዮጵያዊነታቸው ውስጥ አፍሪካዊነት እንዳለ እና የሀገሩ ህዝቦች እንዲህ አስፍተው እንዲመለከቱ ይፈልግ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡
እርሱም ኢትዮጵያዊነት ላንተ ምንድነው? ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ቀላል ነው፤ ቀለል ያለ ሰው መሆን፤ ስለ አፍሪካ የሚያውቅ፤ ስለ አፍሪካ ሥልጣኔ የሚያውቅ፣ ስለ አፍሪካ ባህል የሚያውቅ ሰው መሆን ነው›› ሲል መልሷል፡፡
ኢትዮጵያዊነትን እና አፍሪካዊነትን አንድም ሁለትም መሆናቸውን ጠንቅቆ የሚያውቅ እና በሥነ ጽሑፍ ስራዎቹም ያሳወቀ ነው፡፡
ይቀጥላል