09/10/2022
ዱባይ የቤት ሰራተኞችን በተመለከተ አዲስ ህግ አወጣች
(ቢላል መረጃ ሃሙስ፣ መስከረም 26፣ 2015)
የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሀገር ውስጥ የሰራተኛ መብቶችን ለማጠናከር አዲስ የፌደራል ህግ አዉጥታለች
መስከረም ወር ላይ የወጣው የፌዴራል ሕግ ሁሉንም የቤት ውስጥ የሥራ ሕግ ጉዳዮችን የሚሸፍን ሲሆን የሠራተኞች ፣አሠሪዎች እና ቅጥር ወኪሎችን ግንኙነት በተመለከተ የተለያዩ ድንጋጌዎችን በግልፅ ማስቀመጡን የኤምሬትስ የዜና ወኪል ዋም ዘግቧል ። የአዋጅ ህጉ የስራ ሰአትን፣ ሳምንታዊ እረፍቶችን እና ለቤት ሰራተኞች የሚሰጥ እረፍትን የሚያካትት ሲሆን በህጉ አስፈፃሚ ደንቦች መሰረት የቤት ሰራተኞችን በሳምንት የሚከፈልበት ቀን የማግኘት መብታቸውን ያረጋግጣል።
በሰው ሃብትና ኢሚሬትስ ሚኒስቴር የተላለፉት የስራ አስፈፃሚ ውሳኔዎች የስራ ሰአት እና የእረፍት ጊዜ የመስጠት ሃላፊነት አለባቸው ተብሏል።
በአዋጅ ህግም የቤት ሰራተኞች ከ30 ቀናት ያላነሰ ክፍያ እና የዓመት ዕረፍት የማግኘት መብት እንዳላቸው የተደነገገ ሲሆን የአገልግሎት ጊዜው ከአንድ አመት ያነሰ እና ከስድስት ወር በላይ ከሆነ ሰራተኞች በየወሩ የሁለት ቀናት እረፍት የማግኘት መብት እንዳላቸዉ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም የቤት ሠራተኞች በዓመት ፈቃድ ወደ አገራቸው ለመጓዝ ከፈለጉ አሠሪዎች የመመለሻ ትኬቶቻቸውን ወጪ በየሁለት ዓመቱ መሸፈን እንዳለባቸው በህጉ ላይ ተደንግጓል።
የድንጋጌ ህጉ የቤት ሰራተኞች በኮንትራት አመት ውስጥ ከ30 ቀናት ላልበለጠ ጊዜ የሕመም እረፍት የማግኘት መብታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን የሃገሪቱ ጤና ጥበቃ ባለስልጣን ባወጣው የህክምና ዘገባ መሰረትም ፈቃዱ አስፈላጊ ከሆነ ይቀጥላል ብሏል።
በተጨማሪም የቤት ሠራተኞች በሚኒስቴሩ በወጣዉ አሰራር መሰረት የአሰሪያቸዉን ሃላፊነት ከተወጡ አሰሪያቸውን የመቀየር መብት እንዳላቸዉ በአዋጁ ተካቷል።
ቅጥር ወኪሎችም ወደ ሀገር ከመግባታቸው ከ30 ቀናት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ለቤት ሰራተኞች አስፈላጊውን የህክምና ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸዉ ተገልጿል።
‘’የቤት ሰራተኞችን ሰብዓዊነት በተሞላበት መንገድ መያዝ አለባቸው እንጂ ለጥቃት አያጋልጡም’’ ሲልም ነዉ አዋጁ ፤ አፅንዖት የሰጠዉ።
በአዋጁ ህግ አስፈፃሚ ደንብ እና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውሳኔዎች መሰረት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፈቃድ ሳያገኙ የቤት ሰራተኞችን በቋሚም ሆነ በጊዜያዊነት መቅጠር በህጉ ተከልክሏል።
እንዲሁም የቤት ሰራተኞች በዘር፣ በሀይማኖት፣ በአካል ጉዳተኝነት መገለል ሊደርስባቸው አይችልም የተባለ ሲሆን ጾታዊ ትንኮሳ፣ አካላዊም እና ስነልቦናዊ ጉዳት እንድሁም በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ምድብ ውስጥ ያሉ ማንኛቸውም ድርጊቶችን መፈጸም በህጉ የተከለከለ መሆኑን የአረብ ኒዉስ ዘገባ አመላክቷል።
በፈረንጆቹ ባሰለፍነዉ መስከረም 9 ላይ የወጣው ህግ በኦፊሴላዊው ጋዜጣ ውስጥ ከታተመበት ቀን ከሶስት ወራት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
(በመዲና ጣሰው)