14/07/2026
ዘ-አከልዳማ
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከጥንስስ እስከ ፍጻሜ
(ከ2013-2015 ዓ.ም)
የታሪክ ማስታወሻ
በ ደሳለኝ ዳቼ ኡልቴ (ብ/ጀኔራል)
2017 ዓ.ም
ይህንን ወቅታዊና ለትውልዱ ትምህርት ሰጪ መጽኃፍ በዲጂታልም ሆነ በወረቀት ፕርንት ህትመቱን ስፖንሰር ያድርጉ!
ወይም አሳትመው ለማሰራጨት ፍላጎቱ ካለዎት በውስጥ መስመር ጸሃፊውን ያናግሩት!
መግቢያ
አብዛኞች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰሜኑን ጦርነት "የትግራይ ጦርነት" እያሉ ሲዘግቡትና ሲጠሩት ነበር፡፡ በጣም በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው የ"ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት" በሚል ስያሜ የሚጠሩት፡፡ በጸኃፊው እይታ የእነዚያ፣ የአናሳዎቹ ስያሜ በትክክል ጦርነቱን ይገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም የጦርነቱ መነሻ እና መዳረሻው ከትግራይ ጀምሮ ሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ያካለለ በመሆኑ፡፡ ጦርነቱ የተጀመረው በትግራይ መሬት ይሁን እንጂ አድማሱ እየሰፋ መጥቶ በአማራ፣በአፋርና በኤርትራ መሬትም ተካሂዶ በእነዚህ አካባቢዎች በሚኖሩ ህዝቦች ላይ ዘላቂ ጉዳት አድርሷል፡፡
የሰው ልጅ ደም እንደጎርፍ የፈሰሰበት፣ አጥንት በገፍ የተከሰከሰበት፣ሀብት የወደመበት፣ መረን የለቀቀ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሰቅጣጭ የጦር ወንጀል የተፈጸመበት፣ዜጎች በግፍ ከቀያያቸው የተሰደዱበት…መሬቱ በደም የጨቀየበት፣ የሰው ልጅ አስከሬን ቀባሪ ያጣበት የመጨረሻ አስቀያሚ ጦርነት ነው የሰሜኑ ጦርነት!
ጦርነቱ ሌላም መጠሪያ ሊሰጠው ይችላል፡፡ "5ኛው" ጦርነት የሚል፡፡ ሀገር ያተራመሰው የመጀመሪያው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በዘመነ መሳፊንት ተካሂዷል፡፡ በአጼ ምኒሊክ አሸናፊነት ተደምድሞ ነገር ግን ቁርሾው ለዛሬው 5ኛ ጦርነት ተርፏል፡፡ ሁለተኛው ጦርነት በዘመነ አጼ ሀይሌ ስላሴ ዘመን በትግራይ መሬት ተካሂዶ ተከታታይ የወያኔ አመጾችን ፈልፍሎ በማቆጥቆጥ አልፏል፡፡ ሶስተኛው ጦርነት በደርግ ዘመን ለ17 አመታት ተካሂዶ ከአንድ መቶ ሀያ ሺህ በላይ የኢትዮጵያ እና የትግራይ ወጣቶች በልቶ ወያኔ በስልጣን በቆየባቸው ከ1984-2018 ድረስ ጋብ ያለ መስሎ፤ በአመድ የተሸፈነ ፍም ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡ አራትኛው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ነው፡፡ ከ60 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ወጣት ልጆች ተገብሮበታል፡፡ 5ኛው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት 2013 ዓ.ም በህ.ወ.ሃ.ት እና በለውጥ ሀይሎች መካከል በተፈጠረው የፖለቲካ አለመግባባት የተለኮሰውና አንድ ሚሊዩን የሚያህል የኢትዮጵያ አምራች ዜጎች ያለቁበት፤ በትሪሊዩን ብር የሚገመት ሀብት ንብረት የወደመበት፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተሰደዱበት ጦርነት ሆኖ አልፏል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ስድስተኛው ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋት እና ምኞት አላቸው፡፡ አያደርገው እንዳይባል በአማራ ክልል የተጀመረው አመጽ እና ውጊያ የሰሜኑ ጦርነት አካል ሆኖ ተከስቷል፡፡ በዚህ ስራ ለመዳሰስ ግን ጊዜው ገና በመሆኑ ታልፏል፡፡
5ኛው ጦርነት ከልዩ ልዩ ሙያዎች አንጻር የየዘርፉ ተመራማሪዎች የየራሳቸውን ቀመር ሊያወጡለት የሚችሉበት ነው፡፡ ከፖለቲካ ከወታደራዊ እና ከብሔራዊ ደህንነት አንጻር ከዚህ ጦርነት መጪው ትውልድ መማር ያለበትን ትምህርት መቀመር ተገቢ ነው፡፡ ጸሃፊው እንደ መከላከያ ሰራዊት ጄነራል መኮንን ስለ ጦርነቱ ያለውን ምልከታዎች፣ ትዝብቶች፣ስሜቶች፣ ስህተቶችና ለወደፊት መማር የሚገባንን ትምህርቶች መቀመር የሚያስችሉ መሬጃዎችን የጦርነቱ ሰለባ ለሆነው ህዝብ ማሳወቅ እና ለመጪው ትውልድ ማስተማር ታሪካዊ ሀላፊነት እንዳለበት ስለተሰማው ገና የሰሜን ዕዝ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በተጠቃ ማግስት ጀምሮ መረጃዎችን ሲያጠናቅር ቆይቷል፡፡
በዚህ ጥንቅር የጦርነቱ መነሻ፣ተዋንያንና ዓላማዎቻቸው፣ጦርነቱ ላይ የዋሉ ስትራቴጂዎች እና ታክቲኮች፣ የጦርነቱ አሸናፊ፣የሰላም ጥረቶች፣የጦርነቱ ውጤት እና የመሳሰሉ መሬጃዎችን ከልዩ ልዩ የመረጃ ምንጮች አጠናቅሮ ተንትኖታል፡፡
በአሁኑ ዘመን 90 ከመቶ የሚሆነው መረጃ የሚገኛው ከካሊዕ የመረጃ ምንጮች ነው፡፡ ይህ ማለት ከሌሎች የመረጃ ምንጮች የሚገኘው መረጃ አስር ከመቶ ስለሚይዝ ለግልጽ መረጃዎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ግልጽ መረጃዎች የተፋላሚዎችን ጠንካራና ደካማ ቋጠሮዎች፣የሚከተሉትን ስልትና ስትራቴጂ እና ፍላጎታቸውን…ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡ ስለሆነም ይህ መጽሃፍ በዋናነት ካሊዕ የመረጃ ምንጮችን ዋቢ አድርጓል፡፡
ጸሃፊው መጽሐፉን ሲያበረክት የጦርነቱ መረጃዎቹ የተሟጠጡ ናቸው በሚል ሳይሆን ሌሎች ጸሃፍትና ተመራማሪዎችን ማነሳሳት ይችል ዘንድ መነሻ የሚሆነ ሃሳብ ለማቅረብ ያህል ነው፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ከወታደራዊ፣ ከፖለቲካዊ፣ከኢኮኖሚያዊ፣ ከማህበራዊ፣ ከስነ ልቦናዊ፣ ከስርዓተ ጾታ፣ ከዲፕሎማሲያዊ፣ ከቴክኒካል፣ ከኦፕሬሸናል፣ ከስትራቴጂ፣ ከጂኦ ፖለቲካ ወዘተ አንጻር ተተንትኖ በርካታ መጽሐፍት የሚወጣው ክስተት ስለሆነ በዚህ መጽሐፍ ተሟልቶ ቀርቧል ማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም ሌሎች ተመራማሪዎች እና ጸሐፍት የየራሳቸውን ትንታኔ እንዲያደርጉ ሲጋብዝ በአክብሮት ነው፡፡
መጽሐፉ ስለ ሰሜኑ ጦርነት ለማወቅ ወይም ለመተንተተን ወይም የቀረቡ ሀሳቦችን ለመተቸት ለሚፈልጉ ፖለቲከኞች፣ለጸጥታ እና ደህንነት ሰራተኞች፤ለዘርፉ ሙያተኞች እና ለአጠቃላይ ህዝብ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ የተዘጋጀ ስለሆነ ታሪካዊ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
የመጽሃፉ ይዜት
1. የጦርነቱ ታሪካዊ ዳራ……………………………………………………………………
2. የጦርነቱ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መንስኤዎች?………………………………………
3. የሰሜን ዕዝ መጠቃትና የህግ ማስከበር ዘመቻ (የመጀመሪያ ዙር ጦርነት)……
4. የአማጺው ህ.ወ.ሃ.ት ከተምቤን በረሃ አስከ ሰሜን ሸዋ (ሁለተኛ ዙር ጦርነት)…
5. አማጺው ህ.ወ.ሃ.ት ከሰሜን ሸዋ ወደ መቀሌ ማፈግፈግ (ሶስተኛ ዙር ጦርነት)…………
6. የጦርነቱ የውስጥ ተዋንያን…… …………………………………………………
7. የኤርትራ ተሳትፎና ሚና …………………………………………………………………
8. የውጭ ሀይሎች ተሳትፎና ሚና ……………………………………………………………
9. የጦርነቱ ስትራቴጂያዊ ዓላማዎችና ግቦች ……………………………………………
10. ጥቅም ላይ የዋሉ ወታደራዊ ስትራቴጂዎች………………………………………………
11. ጥቅም ላይ የዋሉ የጦርነት ስልቶች…………………………………….……………
12. በጦርነቱ የፌደራል መንግስት ስትራቴጂክ አቅሞች …………………………………….
13. ስትራቴጂ በንድፈ ሃሳብና በተግባር ……………………………………………………..
14. የጦርነቱ ታክቲኮች ……………………………………………………………………….
15. የጦርነቱ መቋጫ ……………………………………………………………………….
16. የጦርነቱ ውጤት……………………………………………………………………….
17. የሰሜኑን ጦርነት ማን አሸነፈ?…………………………………………………………
18. ከሰሜኑ ጦርነት ምን እንማራለን?……………………………………………………
19. አስረጂ መረጃዎች ………………………………………………………………
20. ዋቢ የመረጃ ምንጮች………………………………………………………………………