24/05/2026
ርዕስ : የተደለዙ ገፆች :- የተካዱ የሕይወት ስንጥቃቶች
ደራሲ : ተስፋዬ ወልደዮሐንስ
ዘውግ : ወግ መድበል
የሕትመት ዓመት : 2018
አጻጻፉ የሚማርክ ፣ በውስጡ ያሉት አስር ታሪኮች እያንዳንዳቸው ማራኪ pacing ያላቸው ፣ ቃላት ውብ ተደርገው የተሰደሩበት ቆንጆ መፅሐፍ ነው።
የደራሲውን መግቢያ ልዋስ!
" የተደለዙ ገፆች " የማይነገሩ ፣ የማይጻፉ ፣ ግን የሚታወሱ ታሪኮቻችን ፣ እነዚህ እውነተኛ ታሪኮች ናቸው። ሁላችንም በኖርነው ሕይወት ውስጥ የኖርናቸውና ሰዎች የኖሩት ግን በሕይወታችንና በሕይወታቸው የማይነገሩ ፣ የማይጻፉ ግን የሚታወሱ ፣ ትዝታቸው በሆኑ አጋጣሚዎች ውልብ የሚሉ የሕይወት የተገነጠሉት ገፆች ፣ የተዘለሉት ገፆች ፣ የተረሱት ገፆች ፣ የደበዘዙት ገፆች ፣ የተደለዙት ገፆች ናቸው። ከታሪካችች ንባብ ውስጥ ባይገቡም ግን ቦታ ያላቸው ፣ አጭር ቢሆኑም በዝርዝር የሚታወሱ ፣ እያንዳንዳቸው ቅፅበት የዛሬን ያክል ፈገግ የሚያስብሉን ፣ የሚያሳዝኑን ፣ የሚወቅሱን ታሪኮች ...!
ከተጻፈው ያልተኖረ የለውም።!!
የመጀመሪያው "በሬ ካራጁ" የተሰኘው አጭር አጭር ታሪክ በደርግ ዘመን የተፈጠረን አንድ ክስተት ያስቃኘናል። በዚህ ታሪክ ውስጥ ገፀ ባህሪያቱ የቤተሰብ ያህል የሚቀራረቡ ናቸው። ነገር የየራሳቸው እምነት ፣ የሚከተሉት ርዕዮት አላቸው። በዚህ መሃል አንዱ ገዳይ አንዱ ተገዳይ ሆነዋል። ገዳይ ሟችን ያውቀዋል። ማቿ በዚያች ቅፅበት ሊገደል እንደሆነ አያውቅም። ሁለቱም በስፍራው የተገኙት የየራሳቸውን ዕጣ ፈንታ ተከትለው ነው። ይተኩሳል። ነገር ግን በተዓምር ይድናል።
በዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ የምንማረው የሞራል ትምህርት አለ። ዋናውን ነገር የምታገኙት ከመፅሐፉ ነው። ይነበብ።
ሁለተኛው ታሪክ ደግሞ :- "የሞትን ጽዋ"
ሰዎቹ የሚፈትን ነገር ውስጥ ናቸው። የሚወዱት ለአንዷ ከነፍሷ የምትወደው ባሏ ፣ ለአንዷ ደግሞ አምጣ የወለደችው ልጇ ነው። ለአንዱ ደግሞ የምንጊዜም ምርጥ ወዳጁ ነው። ነገር ግን ይህንን ሰው በስቃይ ላይ ሆኖ ማየት ልባቸውን እያደማው ነው። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ የዚህን ሰው ነፍስ ማቋረጥ ከሁሉ ከባድና ፈታኝ ነገር ሆኖባቸዋል።
ከመፅሐፉ ገፆች በጥቂቱ
"የሚወዱትን ሰው ከስቃይ በማዳንና ወደ ሞት በመሸኘት መካከል ያለ የአእምሮ ፣ የአካልና የህሊና ትግል ነው። በህይወት መጀመሪያና መጨረሻ ያለው የታሪክ መስመር ነው።
በህይወት ወደዚህች ምድር የመጡን ሁለት ሰዎች አስቡት፣ አቅደውት፣ አልመውት፣ አልያም በተቃራኒው በድንገት በስህተት ወይም በአጋጣሚ ሊሆን ይችላል። ይህም ሕይወታቸውን በበጎ አልያም በክፉ ቀይረንባቸውም ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ግና በአንድ የማይረሳ የደስታ ትዝታቸውን ማኖሪያ መንገድ የፈጠሩን መዳረሻዎች ነን።
ዘጠኝ ወራትን ካሳለፍንበት ዓለም ወደዚህኛው ዕጣ ፈንታችንን ስንመዝ የት መወለድ እንደቻልን እንጂ የት እንደምንሞት ሳናውቅ ነው። የፈጠሩን ሰዎች የነበራቸውንና ያላቸውን ነባራዊ ሁኔታ ሳናውቅ በፍልስፍናቸው ሊያኖሩን ፣ በስነልቦናቸው ሊቀርጹን፣ በእሴቶቻቸው ሊያውቆሙን የሚታተሩበትን የደስታና ፈተና ዓመታት ይጀምሩታል።
እኛም በተቀደደልን ቦይ፤ በተሰፈረልን ቁና ፤ በተሰፋልን ልብስ ልክ የአንዳቸውን ወይም የሁለቱንም ተፅዕኖና ምሳሌነት ፣ጠላትና ወዳጅነት፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ ተስፋና አቅመ ቢስነት፣ ብርሃንና ጨለማ ወዘተ ዛሬና ነገ ይዘን እንጓዛለን። የሰበኩትን በር ሀ ብለው ባስመሩልን ቀጭን መንገድ ይዘን እንጓዛለን።
የብዙዎቻችን የስኬት መንገድ አንደኛ ደረጃ መማር፤ ሁለተኛ ደረጃ መማር፣ ፍላጎትና ምርጫችን ባልሆነ መንገድ በመረጥነው ሙያ መማር፤ መመረቅ ፣ትዳር መያዝ፣ ልጅ ወይም ልጆች መውለድ፣ የልጅ ልጆች ማሳየት፣ መደጋገም ሌላ ትዝታ መፍጠሪያ ማስቀመጥ።
እንደዚህኛው ዓይነት ገጠመኝ ሲሆን ደግሞ፤ ስቃይን ህመምን ሸሽተትን የሚያመጣ መፈተን ሲሆን ደግሞ፤ ለዘመናት አብሮ የኖረ ትንፋሽ፤ ሳቅ፤ ህዘን፤ ደስታ፤ የሚገታ ሲሆን ደግሞ፤ ተፈጥሮ ሌላኛው ሰው የህልሙ ሳይሆን የጉዞ አካል ብቻ እንዲሆን ስታስገድድ ልዩ ይሆናል። ተፈጥሮአዊው ሞት ላይ የሚደረገው መውደቅና መነሳት ሌላ ስቃይን፤ ሌላ መሳቀቅን፤ ሌላ ትግልን ለማሸነፍ ሲባል ውሳኔው የአእምሮ፤ የአካልና የህሊና ፈተና ሲሆን፤ ለማዳን፤ ለማትረፍና ለማቆየት ከመፈለግ ጋር ሲጣረስ ህመሙ ከባድ ነው።ለተኛው፡-
ከሟች ነፍስያ ጋር ያለች ያልተመለሰች ጥያቄ ናት። ሟች ምን ይሰማው ይሆን? ሞትን በሌሎች ውሳኔ መቀበል እንዴት አድርጎት ይሆን? ወደዚያኛው ዓለም ከመጓዙ በፊት መከወን የሚፈልጋቸው ጉዳዮች ምን ነበሩ? ስንቶቹ ተሳክተውለት ይሆን? ስንቶቹስ ሜዳ ላይ ናቸው?
ለአንድ ደቂቃ መናገር ቢችል ምን ይናገር ይሆን? መውደድን፤ ፍቅርን፤ መናፈቅን፤ ምስጋናን፤ ጥላቻን፤ ሀዘንን፤ ብስጭትን፤ መከፋትን፤ ስስትን በተመለከተ ምን እየተሰማው ይሆን?
ልቡ ውስጥ ያለውንና አንድ ቀን ጊዜው ሲዋጅ/ሲፈቅድ አደርገዋለሁ እናገረዋለሁ ያለው ምን ይሆን? ለእሱነቱ ሊያቆመው የፈለገው ማስታወሻ፣ ሊዘክረው የወሰነው ጉዳይስ ምን ይሆን? እንዲያውም በዚህ ቅፅበት ምን እያሰበ ይሆን? ወዘተ የሚለውንም አለማወቅ ከውሳኔው ጋር ያለው ተጣርሶ የሚፈጥረው ህመም ከባድ ነው።"
Tesfaye Haile እናመሰግናለን በእውነት ትልቅ ስጦታ ነው!!
Reviewer : አብርሃም ኑናቶ