26/05/2023
በዛሬው ዕለት ሰሞኑን እየተካሄደ ያለውን መስጊዶችን በጅምላ የማፍረስ ሂደት በመቃወም ሀሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ በገለጹ ሙስሊሞች ላይ ከመጠን በላይ ኃይል በመጠቀም የተወሰደው እርምጃ እጅግ አሳዝኖናል። ተቃውሟቸውን በሰላም በሚያሰሙ ንጹሃን ላይ ጥቃት በመሰንዘር የ2 ሙስሊም ወንድሞቻችንን ህይወት መቅጠፍ እና ብዙዎችን ለጉዳት እና ለእስር መዳረግ እጅጉን የሚያሳዝን እና በጽኑ የሚኮነን ነው። ሙስሊሙን ቁጣ ውስጥ የከተተው የመስጊድ ፈረሳ ሂደት በአስቸኳይ ቆሞ ከህዝበ ሙስሊሙ ወኪል ተቋም ጋር ምክክር እንዲደረግ የቀረበው ጥሪ ከባለድርሻ አካላት ምላሽ ባለማግኘቱ ችግሩ እየተባባሰ ሲሆን በመንግስት በኩልም በሰከነ መልኩ ችግሩን መፍታት ሲቻል ወደኃይል እርምጃ መገባቱ እጅጉን አሳዝኖናል።
ከምንጊዜውም በላይ ህዝበ ሙስሊሙ የሚገጥሙትን ችግሮች ከመሪ ተቋሙ ጀርባ በመሰለፍ በእርጋታና በብስለት መከታተል ያለበት ሲሆን ከየትኛውም ወቅት በበለጠ አንድነቱን ማጠናከርና ከጎንዮሽ ቁርቁስ በመራቅ ከመሪ ተቋሙ ምሪት መጠበቅ እንዳለበት ሊታወስ ይገባል። በእንዲህ ዓይነት ወቅቶች ሙስሊሙን ወክሎ አስፈላጊውን የመፍትሄ ሂደት ለመጓዝና ችግሮች በሠላም እንዲፈቱ ለማድረግ መጅሊሱ የሚጫወተው ሚና እጅግ አንገብጋቢ እና ህዝበ ሙስሊሙንም ከብዙ ወቅታዊ ፈተና የሚጠብቅ እንደሆነ አጥብቀን እናምናለን። ከዚህ አንጻር መጅሊሱ ላቋቋመው የችግር ፈቺ ኮሚቴ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር በመስጠት ነገሮችን በእርጋታ መከታተል ይገባል።
መንግስት የተፈጠረውን ችግር የዜጎችን ህይወት በሚቀጥፍ የኃይል እርምጃ ለመፍታት ከመጣር ይልቅ ከህዝበ ሙስሊሙ ወኪል ድርጅትና ከሌሎች የማህበረሰብ መሪዎች ጋር በእርጋታ በመነጋገር ለችግሩ እልባት መስጠት ይኖርበታል። በተለይም በጅምላ እየተፈፀመ ያለውንና ሙስሊሙን እጅግ እያስቆጣ ያለውን አሳዛኝ የመስጊድ ፈረሳ ዘመቻ በአስቸኳይ በማስቆም ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ሊጀምር ይገባል።
መስጊዶች ለየትኛውም ከተማ አስፈላጊ መንፈሳዊ ማዕከላት እንደመሆናቸው መጠን ለሸገር ሲቲም ሆነ ለሌላ የትኛውም ግንባታ እንደእንቅፋት ተደርገው መታየታቸው ፍጹም ስህተት ነው። በመሆኑም በግፍ የፈረሱት መስጊዶች በከተማ ፕላኑ ውስጥ የሚገባቸው ቦታ ተሰጥቷቸው ማረጋገጫ ሰነድ ለህዝበ ሙስሊሙ ወኪል ድርጅት መጅሊስ መሰጠት እንዳለበት ለማስታወስ እንወዳለን። ይህ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሊያስማማ የሚገባ የመፍትሄ አቅጣጫ ነው።
በመጨረሻም በተወሰደው አሳዛኝ የኃይል እርምጃ ጉዳት ለደረሰባቸው ፈጣን ማገገም፣ ህይወታቸውን ላጡ ጀነተል ፊርደውስ፣ ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን ይሰጥ ዘንድ አላህን አጥብቀን እየለመንን ህዝበ ሙስሊሙ በመሪ ተቋሙ ዙሪያ በመሰባሰብ ነገሮችን በብስለት እንዲያጤንና እንደሁልጊዜው ሁሉ ችግሩን ከሚያባብሱ አካሄዶች በራቀ መልኩ ለመፍትሄ እንዲንቀሳቀስ አደራ እንላለን!